Ubuntu Amharic

ትዕይንተ-ዑቡንቱ

ትዕይንተ ዑቡንቱ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፤ የሰው ልጆች እርስበርሳቸው የተሳሰሩ መሆናቸውን በማሳየት በተለይም
በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብና በጎሳዎች መካከል ያለውን ቁርኝት ከአፍሪካ ባህላዊ እሴቶች ጋር በማጣመርና
በመመርመር የሚቀርብ ነው።
ከዚህ ሌላ በዚህ ፕሮግራማችን አፍሪካ ራሷም ሆነ ሌሎችን በመጉዳት የጋራ ከሆነው የሰብዓዊነት መለያዎች
የከሸፈችባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን። የአፍሪካን ሁኔታ በዚህ መልኩ ከዳሰስን በኋላ እያንዳንዳችን እንደ
አፍሪካዊ ለአህጉራችን ሰላም፣ ነጻነትና ፍትሕ እንዲሰፍን ምን ማድረግ እንዳለብን ለውይይት እናቀርባለን።
ዑቡንቱ አፍሪካዊ ፅንሰሃሳብ ሲሆን በተለይ በደቡብ አፍሪካ የነጻነት፣ የእውነትና የዕርቅ ትግል ወቅት በሊቀጳጳስ
ዴዝሞንድ ቱቱ ዕውቅናው የበለጠ እንዲያንሠራራ ተደርጓል። በዑቡንቱ ሃሳብ ውስጥ ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነና
የእያንዳንዳችን ኅላዌነት እንደ ሰው እንዴት ከሌሎች ጋር ከውልደት እስከ ሞት የተቆራኘ መሆኑ የተካተተ ነው።
ዑቡንቱ የሌሎችን የተፈጥሮ እሴት፣ ክብርና መብቶች በመገንዘብ እያንዳንዱ ሰው ከሰብዓዊ ፍጡር በሚልቅና ከማንም
ጋር ሊወዳደር በማይችል ፈጣሪ አምላክ አምሳያነት የተፈጠረ መሆኑን በመገንዘብ፤ ይህ መረዳት የሰው ልጆችን ግንኙነት
እንዴት ለበጎ እንደሚቀርጸው ትኩረት ይሰጣል።
ዑቡንቱ እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር ለሌላኛው መኖር አስፈላጊ እንደሆነ ትኩረት ይሰጣል፤ ከዚህ ባሻገርም የአንዱ
ሰብዓዊነት የሚረጋገጠው ከሌላው ጋር ባለው ግንኙነት እንደሆነ ሃሳብ ይሰጣል። ስንወለድ በራሳችን ማድረግም ሆነ
መቆም፤ ብቻችንም መከወን አንችልም፤ ለዚህ ነው ወደዚህች ዓለም ስንመጣ የተዘረጉ እጆች የሚቀበሉን። በህይወት
ጉዟችን ቤተሰባችን እና ማኅበረሰባችን ቀዳሚ በመሆን ተንከባክበው ያሳድጉናል፤ ቋንቋ፣ ባህል፣ ባህርያት እና ሌሎች
እሴቶችን ያበረክቱልናል። ከዚያም በህይወት ጉዟችን እጅግ ብዙ እየተቀበልን እንሄዳለን። ስንሞት ሌሎች የተዘረጉ እጆች
ይቀበሉና ይሸኙናል፤ በራሳችን ማድረግ አንችልምና።
በዚህ ዓይነት ሁኔታ እርስበርሱ በተጣመረ ዓለም ውስጥ አንድ ሰው የሚያደርገውም ሆነ የማያደርገው ነገር ለክፉም
ይሁን ለበጎ የጎላ ልዩነት ያመጣል።
ዑቡንቱ ሌሎችን “እነርሱ” በማለት ሳይሆን “እኛ” ብሎ ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት ከሰብዓዊ ፍጡር ጋር ትክክለኛና
ግብረገባዊ ግንኙነት መመሥረት ማለት ነው። “የይቅርታ መጽሐፍ” (The Book of Forgiving) በሚለው
መጽሐፋቸው ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ እንዲህ ይላሉ፤ “በደቡብ አፍሪካ ዑቡንቱ ማለት ዓለምን የምናስተውልበት መንገድ
ነው፤ የጥሬ ቃሉ ትርጉም “ሰብዓዊነት” ማለት ነው፤ … ሰብዓዊ ማንነታችን እርስበርስ የተቆራኘ ነው፤ ስለዚህ በዚህ የተቀየጠ
ማንነታችን ውስጥ አንዲት ክር ከተበጠሰች መልሰን በመቋጠርና በመጠገን ውህደታችን አስቀጥለን ምሉዕ ማድረግ
ይገባናል።”
ስለዚህ በዑቡንቱ ትዕይንት ከሌሎች ተጋባዥ ዕንግዶች በተጨማሪ የአፍሪካውያንን ድምጽ መስማት እንፈልጋለን፤ ይህንን
ስናደርግ ሦስት ነገሮችን እንመረምራለን፤ 1) በዑቡንቱ መርህ የእያንዳንዱን ሰብዓዊ ፍጡር እሴት በማክበር መኖር
ውስጥ ያለው ትክክለኛ አካሄድ የትኛው ነው? 2) በአሁኑ ወቅት ያጣነው ነገር ምንድነው? ይህንን መርህ ተከትለን
ከመኖር የከሸፍነው የት እና እንዴት ነው? 3) ይህንን አስፈላጊ መርህ ወደነበረበት በመመለስ ለአህጉራችን
ግብረገብነትን፣ ቅን አኗኗርን፣ ዕርቅን እና ሰላምን ለሁሉም እንዲሰፍን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
በዑቡንቱ መርህ መኖር የሚጠቅመው ከእኛ ማዕቀፍ ውጪ ካሉት ይልቅ ቤተሰባችንና ማኅበረሰባችንን ነው። ስለዚህ
በማኅበረሰባችን ውስጥ የተከሰቱትን ክፍፍሎችና ስብርባሪዎች እንዴት ነው መጠገን የምንችለው? በዘር፣ በቆዳ
ቀለም፣ በሃይማኖት፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሁሉ ከሰብዓዊነት ተራ እንድንወርድ የሚያደርገንን መሰናክል
ሁሉ እንዴት ነው ማሸነፍ የምንችለው? “እኔን” በ“አንተ” ውስጥ “አንተ”ን ደግሞ በ“እኔ” ውስጥ ማየት
የሚያስችለን ምንድነው? ፈጣሪ አምላካችን ይህንን ህይወት እንዴት መኖር እንዳለብን የሚፈልገውስ ምንድነው?
ይህ የዑቡንቱ ትዕይንት ስለሌላው እንድናወራ ሳይሆን እርስበርሳችን እንድንነጋገር ጅማሬ ይሰጠናል፤ ይህ ደግሞ
በአፍሪካችን የታወቀውንና በተለምዶ በተግባር የዋለውን ለሌሎች የማካፈልና ለሌሎች የመጠንቀቅ ዓለምአቀፋዊ
የእውነት መርህ ነው – ዑቡንቱ!